የአበባ እና የፍራፍሬ እርሻዎች መረጃ ክፍተትን ለማሟላት የሚያችል ጥናት ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው

የኢትየጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የአበባ እና የፍራፍሬ እርሻዎች ጥናትን ለማካሄድ ለ10 ቅ/ጽ/ቤት ሃላፊዎች፣10 ስታቲስቲሽያኖች፣10 ፕሮግራመሮች፣15 ተቆጣጣሪዎችና ለ30 መረጃ ሰብሳቢዎች ከየካቲት 06 እስከ የካቲቲት 10/2014ዓ.ም በአዳማ ፓን አፍሪክ ሆቴል ስልጠና ሰጠ፡፡

ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የተቋሙ ምክትል ዋና ዳሬክተር አቶ አማረ ለገሰ የአበባና ፍራፍሬ ምርቶች የውጪ ምንዛሬን በሰፊው የሚያስገኙ ስለሆነ የተደራጀ ስታቲስቲካዊ መረጃ ስለዘርፉ መኖር እንዳለበትና መንግስትም ለዚህ ክፍለ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የአበባና ፍራፍሬ አምራቾችን ማዕከል ያደረገ የልማት ስትራቴጂ በመንደፍ በአሁኑ ወቅት ያለውን ምርትና ምርታማነቱን ለማሻሻልና ደረጃውን ከፍ ለማድረግ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው ከዚህ ጥናት የሚገኙ ስታቲስቲካዊ መረጃዎች ይህ እርሻ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ያለውን አስተዋፆ ለመገምገም እና እንዲሁም መንግስትም ወደፊት  ለሚያወጣቸው ግብርናውን ያማከሉ  ዕቅዶችና ፖሊሲዎች አይነተኛ እና ወሳኝ ሚና እንደሚያበረክት ተናግረዋል፡፡

ጥናቱ እንደመነሻነት በ10 ቅ/ጽ/ቤቶች እንደሚሰራ ግልጸው መረጃዎቹ የሃገሪቱን የአስር አመት የልማት ዕቅድ መመለስ አንዳለባቸውና ስታቲስቲሺያኖች፣ ተቆጣጣሪዎችና መረጃ ሰብሳቢዎች መረጃዎቹን በጥራት፣ በብቃትና በወቅቱ ለመሰብሰብ የቅንጅት ስራ መስራት እንዳለባቸው ም/ዋ/ዳሩ አሳስበዋል።

ከጥናቱ የአበባ ምርት እና የኤክስፖርት  ምርት  የሆኑት  እንደ  እንጆሪ፣ ወይን የመሳሰሉት  ፍራፍሬ ምርቶች በተመለከተ የምርት መጠን ፣ የለማው የመሬት ስፋት ፣የግብአት ማዳበርያ፣ ኬሚካል፣ መድሀኒቶች አጠቃቀም፣ ሥራ ከመጀመርና ከተጀመረ በኋላ ያጋጠሙ ችግሮች፣ ጥቅምላይ የዋሉ የእርሻ መሳርያዎች ዓይነት፣ ብዛትና መሰል መረጃዎች ይሰበሰባሉ፡፡

የጥናቱን ውጤት በዋናነት መንግስት ለሚያካሂዳቸው አዳዲስ ፖሊሲዎችና የረዥምና ለአጭር ጊዜ ዕቅዶችና በዘርፉ ያለውን የኤክስፖርት መጠን፣ የታረሰ የመሬት ስፋት፣ ምርትና ምርታማነት ለማወቅ የሚጠቀምበት ሲሆን፣ በዘርፉ ለተሰማሩ ኢንቬስተሮችና ተመራማሪዎች ለምርምርና ጥናቶቻቸው እንደመነሻ ግብዓትነት ያገለግላል፡፡ በተጨማሪም በሀገሪቱ በአበባና ፍራፍሬ እርሻ ድርጅቶች የተመረተውን አጠቃላይ የአበባ ፍራፍሬ ምርት መጠን ፣በምርቱ የተሸፈነ የመሬት ስፋት ፣ከአንድ ሄክታር የሚገኘውን ምርት ፣ከዓመት ወደ ዓመት ያለውን የአበባና ፍራፍሬ ምርት መጠንና የታረሰ መሬት ስፋት ለውጥ፣ የእርሻ ሥራ አጠቃላይ ሁኔታ ጥቅም ላይ የዋለ የማዳበሪያ፣ የፀረ-ሰብል መድሀኒት ዓይነትና መጠን እንዱሁም የመስኖ አጠቃቀም ለማወቅ የሚያስችል መረጃ ያስገኛል።